Girma Bèyènè & Akalé Wubé ‎– Éthiopiques 30: “Mistakes On Purpose

  1. ትወጂኝ እንደሁ (አሁን ንገሪኝ)
  2. እኔ ነኝ ባይ ማነሽ
  3. ሙዚቃዊ ስልት
  4. እንከን የሌለብሽ
  5. በመልክሽ አይደለም
  6. ፍቅር እንደክራር (ይበቃኛል)
  7. መስሎኝ ነበር
  8. ፍፁም ፍፁም (ጥሩልኝ ቶሎ)
  9. ለአምሃ (ለአምሃ እሸቴ)
  10. ሴት አላምንም
  11. ውብ ናት
  12. መለወጥሽ ምነው
  13. ፅጌረዳ
  14. ትወጂኝ እንደው (አሁን ንገሪኝ) [malus track

በ2007 አ.ም ይህ (አልበም ከመውጣቱ በፊት) ከግርማ ጋር ተገናኝተን ብዙ ብዙ ተጨዋውተን ነበር:: ጨዋታችንን ተከትሎ በወቅቱ mikimacviews የተባለው ብሎጌ ላይ ያሰፈርኩትን እንዳለ ላምጣላችሁ::

ግርማ በየነ ማነው?
እንደ መንደርደሪያ

ግርማ በየነ በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ላቅ ያለ ድርሻ የበረከተ አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ሲሆን፤በአጋጣሚ ተገናኝተን አንዳንድ ነገሮችን አወራን፤እናም አንድ ነገር ወደውስጤ መጣ። ይህን ሰው ግን ማነው በደምብ የሚያውቀው? እውነት በሰራው ልክ ክብር ሰጥተነው ይሆን?መልሱን ለናንተው ትቻለሁ። እናም በራሴ የማውቃቸውን አንዳንድ ታሪኮች ላጫውታችሁ ወደድኩ።ማስተካከያ ካለ በደስታ እቀበላለሁ።

እንደአብዛኞቹ የታሪክ ጸሀፊዎች እዚህ ተወለደ፣እዚህ ተማረ፣እዚህ አደገ የሚለውን እንተወው እና ስለ ግርማ የማውቀውን ትንሽ ልበላችሁ::

ሰኔ 2007 ዓ.ም
መጻፍ ስጀምር…(ይኸው)
ግርማ በየነ በቀደመው ትውልድ እንጂ በአሁኑ ትውልድ እምብዛም ባይታወቅም ከ1952-1970 ባሉት አመታት በተጫወታቸውና ለታሪክም ሆነ ለትውልድ ባበረከታቸው የጥበብ ስራዎቹ የማያደንቀውም ሆነ የማይደሰት የሙዚቃ አፍቃሪ የለም። ግርማ በየነ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሙዚቃው አለም ብቅ ያለው በወቅቱ ተማሪ ነበርና፣ በክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ቴአትር ቤት ወይም በአሁኑ ብሄራዊ ቴአትር በ1952 የዘመን መለወጫ በአል ላይ የቅርብ ጔደኛው ከነበረው ግርማ ቦጋለ ጋር በመሆን ቦክስ ጊታር እየተጫወተ ባቀረበው ሙዚቃ ነበር። ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ባደረበት ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ ፍቅር የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ በቴአትር ቤቱ በጊዜአዊነት በመቀጠር ወደ ሙዚቃው አለም በመቀላቀል በቴአትር ቤቱ ለ1 አመት ከ3 ወራት ያህል አገልግሎአል።

በመቀጠልም ከቴአትር ቤቱ ለቆ በመውጣት ወደ ራስ ሆቴል በማምራት ከቅርብ ጔደኞቹ ጋር በመሆን ራስ ባንድ የተባለ ባንድ በማቌቌም እና ዘወትር አርብ ምሽት የተለያዩ የሀገር ውስጥና የባህር ማዶ ሙዚቃዎችን በመጫወት ለበርካታ ጊዚያት ሰርቶአል። ከተወሰነ ጊዜ በኌላ የባንዱ አባላት ስማቸውን ግዮን ባንድ ብለው በመቀየር ወደ ግዮን ሆቴል ሲዛወሩ ግርማ ከሌሎች ወዳጆቹ ጋር በመሆን ራስ ባንድን እዚያው ራስ ሆቴል ይዞ ሊቀር ችሎአል። በዚህ በ2ኛው ራስ ባንድ ውስጥ ከነበሩትም መካከል
ራሱ ግርማ በየነ ፒያኖ፣
ተስፋማርያም ኪዳኔ ሳክስፎን፣
ፈለቀ ኪዳኔ ትራምፔት፣
ሀይሉ ከበደ (ዝሆን) ቤዝ ጊታር፣
ግርማ ዘማርያም ድራም
እንዲሁም ምኒልክ ወስናቸውና ሰይፉ ዮሃንስ የባንዱ ዋና ድምጻውያን ነበሩ።

በዚህ ባንድ ውስጥም በመሪነት ከማገልገሉ በተጨማሪ በድምጻዊነት፣በጊታር፣ፒያኖ እና ድራም ተጫዋችነት፣በግጥም እና ዜማ ደራሲነት እስከ 1957 አ.ም ድረስ አገልግሎአል።

ራስ ባንድ ከተበተነ በኌላም ቢሆን ግርማ በየነ በሌሎች ባንዶች ውስጥ ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ ፍላጎቱ የራሱን የሆነ ባንድ ለማቌቌም ነበርና ፤«ዘ-ግርማስ ባንድ» (ግርማ በየነ እና ግርማ ቦጋለ) የተባለውን ባንድ መስርቶ ጽጌሬዳ፣ቁርጡን ንገሪኝ፣ጥሩልኝ ቶሎ የተሰኙትን ሙዚቃዎች ደርሶአል አቀናብሮዋል)።
ከባንዱ አባላት ውስጥም
ራሱ ግርማ በየነ፣
አየለ አራርሶ፣
ጌታቸው ደገፉ እና
ተስፋማርያም ኪዳነማርያም ዋነኞቹ ናቸው።
«ዘ-ግርማስ ባንድ» ለኢትዮ ስታር ባንድ መመስረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ይነገራል።ከዚያም በመቀጠል ከአለማየሁ እሸቴ ጋር በመሆን «አለም-ግርማ» የተባለ ባንድ መስርተው ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል።

ምንም እንኴን ብዙዎቻችን ግርማ በየነ ከድምጻዊነት ባለፈ የባለብዙ ተሰጥኦ ባለቤትነቱን ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ሙዚቃዎችን እንኴን እንደሰራ ባናውቅም ነገር ግን የግርማን ስራዎች ለማወቅ ከፈለግን በፈረንሳያዊው የሙዚቃ ፕሮዲውሰር እና አክቲቪስት ፍራንሴዝ ፋልሴቶ ቡዳ ሬከርድስ የታተሙትን ኢትዮጲክስ የተባሉትን የሙዚቃ ስብስቦች ማየት ብቻ በቂ ነው። በሀገራችን የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በዋነኝነት የሚታወቀው ሙላቱ አስታጥቄ በነዚህ አልበሞች ውስጥ ወደ 41 የሚደርሱ ስራዎችን የሰራ ሲሆን ግርማ በየነ ደግሞ ከ60 በላይ ስራዎችን ሰርቶዋል። ከነዚህም ስራዎቹ ውስጥ
አዲስ አበባ ቤቴ፣
የወይን ሀረጊቱ፣
ተረድቼዋለሁ፣
ማን ይሆን ትልቅ ሰው፣
እሩቅ ያለሺው፣
አልተለየሺኝም፣
ሸጊቱ ማሬ፣
ህይወቴ አባቴ ነው፣
ቆጨኝ መሳሳቴ፣
ትላንትና ዛሬ፣
ተጭሮ አዳሪ ነኝ፣
እስከጊዜው በርቺ
እና አያልቅም ተደንቆ… ሌላም ብዙ ብዙ ብዙዙዙዙዙዙ . . .

ከዚህም በተጨማሪ በ1962 ዓ.ም በአምሃ ሬከርድስ ያስቀረጻቸውን እና በዋነኝነት በድምጻዊነት የሚታወቅባቸውን አራቱን ሙዚቃዎቹን እንመልከት።

  1. «ሴት አላምንም» ግጥምና ዜማውን እንዲሁም አብዛኛውን የሙዚቃውን ሀሳብ ያዋጣው ራሱ ግርማ በየነ ሲሆን ሙላቱ አስታጥቄ አቀናብሮታል።
  2. «እንከን የሌለብሽ» ግጥሙን የሰጠው ታዋቂ ፒያኖ ተጫዋች የነበረውና የኢትዮጲያ አየር መንገድ የበረራ ሙዚቃዎች ተብለው የሚጠሩትን በመሳሪያ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎች ያቀናበረው ግርማ ደገፉ ሲሆን ዜማውን እና ሙዚቃውን በከፊል እራሱ ግርማ በየነ፤በማቀናበሩ ደግሞ ሙላቱ አስታጥቄ
  3. «እኔ ነኝ ባይ ማነሽ? » ግጥም ግርማ ደገፉ ዜማ ግርማ በየነ የማቀናበር ስራውን ሙላቱ አስታጥቄ
  4. «ይበቃኛል(ፍቅር እንደ ክራር)» ግጥምና ዜማ ባህታ ገብረህይወት ቅንብሩን ራሱ ግርማ በየነ ሰርቶታል።

እነዚህ አራት ሙዚቃዎች ከኢትዮፒክስ የአልበም ስብስብ ውስጥ Ethiopiques 8: Swinging Addis በተባለው አልበም ውስጥ ይገኛሉ።
በተጨማሪ ኢትዮጲክስ 22 ላይ ያሉት 18 የአለማየሁ እሸቴ ሙዚቃዎችም ሁሉም የተሰሩት በግርማ በየነ አቀናባሪነት ነው::

ከ1967 አብዮት በኌላ እንደነ ጥላሁን ገሰሰ፣ሂሩት በቀለ፣አለማየሁ እሸቴ፣ብዙነሽ በቀለ ያሉ በርካታ ሙዚቀኞች አብዮት ነክ ዜማዎችን እንዲጫወቱ ይገደዱ ነበር።ይህም ጊዜ አስከፊው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን እንደነበር ራሱ ግርማ ይናገራል።በዚህም የተነሳ እንደ አምሀ ደስታ ያሉ ጎልተው የሚጠቀሱ የሙዚቃ ሰዎች ሀገሪቱን ለቀው ለመሸሽ ተገደው ነበር።ግርማ በየነም በዚህ ወቅት ነበር ዋሊያስ ባንድ የተባለውን ባንድ ለመቀላቀል የበቃው ነገር ግን በዚህ ባንድ ውስጥም ቢሆን አዳዲስ ስራዎችን መስራቱን አላቆመም ነበር።ዋሊያስ ባንድ እያለ ከሰራቸው ሙዚቃዎች መካከል በዋናነት እንደ ኢይዘር ኦርኬስትራ (Either Orchestra) እና ዳክታሪስ (Dactaris) የተሰኙት አለም አቀፍ እና ታዋቂ የሙዚቃ ባንዶች በተደጋጋሚ የተጫወቱትን «ሙዚቃዊ ስልት» የተሰኘውን በመሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃውን መጥቀስ ይቻላል።

በ1974 አ.ም ዋሊያስ ባንድ ወደ አሜሪካን ሀገር ባደረገው የኮንሰርት ጉዞ ወቅት ወደዚያ ካቀኑት ሙዚቀኞች ውስጥ ግርማ በየነ አንዱ ነበር:: የሙዚቃ ዝግጅታቸውን ለ1 አመትያክልበተለያዩ ግዛቶች እየተዘወወሩ ካቀረቡ በሁዋላ ግርማ በየነ እና መላከ ገብሬ እዚያው ለመቆየትና ወደ ኢትዮጵያ ላለመመለስ ወስነው የቀሩ ሲሆን ለዚህ ውሳኔ ያበቃው ደግሞ እጅግ ይወዳት የነበረችው ፍቅረኛው ሞት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። ግርማ በየነ ከሙዚቃው አለም ርቆ ከ30 አመታት በላይ ሰው ሀገር በስደት የቆየ ሲሆን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ኑሮውን እዚህው አዲስ አበባ አድርጔል።

የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤት እና የትውልድ ቅርስ የሆነው ግርማ ዛሬ እርጅና ተጫጭኖታል፣ተጎሳቁሎአል። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ከማንጎራጎር አልቦዘነም። እንደውም ከነአበጋዝ ክብረወርቅ ጋር ሙዚቃ እየሞካከረ እንደሆነ ነገረኝ። በእውነት እጅግ ነው ደስ ያለኝ። እባካችሁ ለሀገር ታሪክ የሰሩ ሰዎችን በቁማቸው አክብረን አጋርነታችን እናሳያቸው። ምናልባት ታሪክ አዛብቼ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ ምንም የጨመርኩት ነገር የለም እንደውም ከዚህ የሚልቀውን ስራውን እንደዘነጋሁበት ነው የሚሰማኝ፤ከብዙ በጥቂቱ ነው የነገርኴችሁ።ለምሳሌ 1957 ከግርማስ ባንድ ጋር ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ቴአትር ቤት ድራም እየተጫወተ እና እየዘፈነ ስላቀረበው ኮንሰርት አልነገርኴችሁም። ምናልባት አንድ ቀን እንመለስበት ይሆናል::


ግርማ በየነ ዛሬ (2020)

ከላይ ያሰፈርኩት ፅሁፍ የዛሬ 5 ወይም 6 አመት የተፃፈ ነው:: ስለ ግርማ በጥቂቱ የማውቃትን እውነት የገለጥኩበት:: ዛሬ ስለግርማ ያለኝ አስተሳሰብ ከዚያም የላቀ ነው:: ግርማ ለእኔ ብዙ ነገር ነው

  • የሙዚቀኝነት ስነ-ምግባር ጥግ (የግርማን ትህትና እና ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚያይበትን ቅንነቱን ላየ ሰው ግርማ ማለት ምን እንደሆነ ይረዳኛል)
  • የዜማ ደራሲ
  • አቀናባሪ
  • ፒያኒስት
  • ጊታሪስት
  • ድራመር
  • የባንድ መሪ
  • ከዘመኑ ቀድሞ የተፈጠረ ድንቅ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ሰው
  • ከምንም በላይ ደግሞ ውለታውን ቅርጥፍ አድርገን የበላነው የሃገር አርማና ሰንደቅ ነው::

የግርማ በየነን ስራዎች እንዘርዝር ከተባለ እስከዛሬ ድረስ የለጠፍኩላችሁን የኢትዮጲክስ አልበሞችን መለስ ብሎ ማየት ብቻውን በቂ ነው:: (በነገራችን ላይ ግርማ የሰራቸውና ኢትዮጲክስ ላይ ያልተካተቱ ሌሎችም ስራዎች አሉ)

ከላይ የፃፍኩት ሃሳብ ላይ ለመቀጠል ያክል ግርማ በየነ ከ30 አመታት የሙዚቃ እረፍት በሁዋላ ዳግም ወደመድረክ ተመልሶዋል:: ለዚህ ታላቅ የሃገር ባለውለታ ወደመድረክ መመለስ ደግሞ የሙዚቃ አክቲቪስትና ፕሮዲውሰር እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነው ፍራንሲስ ፋልሴቶ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል:: እኛ የዘነጋናቸውን የሃገር ባለውለታዎች (በመዳብ የቀየርናቸው ወርቆቻችንን) ሌሎች ሲያከብሩዋቸው ማየት መቼም እኛ ሃገር አዲስ አይደለም:: ፍራንሲስ ከ30 አመታት በሁዋላ ግርማ በስደት ለ30 አመታት ይኖር ወደነበረበት ወደአሜሪካ በማቅናትና ግርማን በማሳመን ወደ ፈረንሳይ ይዞት ተመልሶ አካሌ ውቤ ከተሰኘው የፈረንሳዩ የሙዚቃ ቡድን ጋር ይህንን ኢትዮጲክስ 30 Mistakes on Purpose (በምክንያት የሆነ መሳሳት) የሙዚቃ አልበም እንዲያደርሰን አድርጎታል::

ስለፍራንሴስ ሲነሳ ብዙ አከራካሪ ሃሳቦች ይመጣሉ:: ሙዚቀኞች የልፋታቸውን አላገኙም እሱ ግን ዛሬም በሙዚቃዎቹ ላይ ባለመብት ነው ሲባል ሰምተንም ይሆናል:: ነገር ግን እውነቱን ለመናገር ፍራንሲስ ያኔ አምሃ እሸቴን አሳምኖና ስምምነት አድርጎ እነዚህን ሙዚቃዎች ድጋሚ ባያሳትማቸው ኖሮ ምናልባትም የዚያ ዘመን ሙዚቃ ተረት ሆኖ ይቀር ነበር:: ፍራንሲስ የኢትዮጲክስ አልበሞችን ለማውጣት ያደረገውን ተጋድሎና መሰዋዕትነት ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ደርግ ስልጣን ከመያዙ በፊት የጀመረው እቅዱ 19 አመታት እንደፈጀበትና ያን ያህል ረጅም ዘመን መጠበቁንስ እናውቅ ይሆን?

በቅርቡ Ethiopiques – Revoult of The Soul የሚል የዘመኑን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ግርማ በየነ የከፈለውን መስዋዕትነት ጨምሮ የሚያሳይ አንድ ጥሩ ዘጋቢ ፊልም ተሰርቶዋል:: (የኢትዮጲያን ሙዚቃ እወዳለሁ የሚል ሁሉ ሊያየው የሚገባ ድንቅ አስረጂ ፊልም ነው) በተለይም

  • ግርማ በየነ
  • አምሃ እሸቴ እና
  • ፍራንሲስ ፋልሴቶ
    ለኢትዮጲያ ሙዚቃ ምን እና ምን እንደሆኑ በደምብ የሚያስረዳ ነው::

ለማንኛውም ስለ ግርማ በጥቂቱ ይህን አልኩ እንጂ ሰውየው እንኩዋን ተነቦ የማያልቅ ትልቅ መፅሃፍ ነው:: ሃገር ውለታውን የዘነጋች በስራው ልክ ያላከበርነው የሃገር ጀግና ነው:: እኛ ደግሞ የዚህ ያልተዘከረ ጀግና የታሪክ ባለእዳዎች ነን:: ጀግኖቻችንን በቁም ሳናከብር ህልፈታቸውን ጠብቀን ከንፈር የምንመጥ:: 😢

ለማንኛውም ለዛሬ ለግርማ ረጅም እድሜና ጤና እየተመኘሁለት 30ውን የኢትዮጲክስ አልበሞች ስዳስስ የከረምኩበትን ፕሮጀክትም በዚሁ አበቃሁ::
ከቻላችሁ ይህንን ፅሁፍ ለወዳጆቻችሁ አጋሩት::

··················

Comments

One response to “Girma Bèyènè & Akalé Wubé ‎– Éthiopiques 30: “Mistakes On Purpose”

  1. Merid Avatar

    It’s very interesting I remember Girma Beyene his songs is still so nice .

    Like

Leave a comment