Orchestra Ethiopia ‎– Éthiopiques 23

Orchestra Ethiopia ‎– Éthiopiques 23

1- ትዝታ
2- ትንሽ መከዳ
3- ማሚትና ከበደ
4- ሆዴ
5- ከቶ አይቀርም ሞቱ
6- ዳቸና ኮባ
7- መዲናና ዘለሰኛ
8- ሸጊቱ
9- የህፃኑ ልቅሶ
10- ሄላውሾ
11- ለቅዳሜ አጥቢያ
12- ብስጭት
13- ላሌ ጉማ
14- ወላይታ ጊታር
15- ደርባቤ
16- አባ ባላኖ ሻንካ
17- ስንብት
18- ጎራው
19- ሸብ ሮቤ
20- ኦድ
21- ሻማ ከፈና
22- ተራራው
23- ስምሽ ማነው?

ይህ 23 ሙዚቃዎችን የያዘው 23ኛው አልበም የወጣው በ1999 አ.ም ሲሆን በኢትዮጵያ የባህላዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በርካታ ሙዚቀኞችን በመያዝ የተደራጀ በነበረው በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ የተሰሩ ሙዚቃዎችን የያዘ ነው::

ተስፋዬ ለማ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ የሚለው መፅሃፉ ላይ ስለ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እንዲህ ይላል::

“የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እስኪቋቋም ድረስ በባህል ሙዚቃ ጥሩ እውቀት ያላቸውን ሙዚቀኞች በማሰባሰብ በ1960 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቤተ ኪነጥበባት ወቴያትር ሥር ተቋቋመ። ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ሲወጠን ዋና ዓላማው ወደፊት በጥናት ላይ ለሚመሠረተው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ማደራጃ እንዲሆን ነበር። የዚህ የሙዚቃ ቡድን መሥራችም በትውልድ ግብፃዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት ከፍተኛ የሙዚቃ ባለሙያ ፕሮፌሰር ሐሊም ኤልድሃብ ነበሩ።

ለአንድ ሃገር ዩኒቨርሲቲ ከሚያስፈልጉና ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው መሠረታዊ የጥናት መስኮች አንዱ ባህል ነው። በመሆኑም ኪነ ጥበባት ወቴያትርን ለማቋቋም ከአሜሪካ የመጡት ሶሥት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ፕሮፌሰር ፊሊፕ ካፕላን፣ ማርሻል ጆን ኮክስና ፕሮፌሰር ሐሊም ኤልድሃብ በካርኔጊ ድርጅት ረዳትነት ይህንኑ ማዕከል በከፍተኛ ደረጃ ለማቋቋም ተዘጋጅተው ነበር። ሆኖም በዘመኑ የነበሩት የዩኒቨርሲቲው ባለሥልጣናት ዐቢይ ትኩረታቸው ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እንጂ ለዘፈንና ለቴያትር አለመሆኑን በማስታወቃቸው በትልቁ ታስቦ የነበረው የዩኒቨርሲቲው የባህል ተቋም ሊጨናገፍ ችሏል። ለዚሁ ጉዳይ የመጡት ባለሙያዎችም ተስፋ ቆርጠው ወደ ሃገራቸው ተመለሱ።

የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የሙዚቃ ቡድን ሲመሠረት የተሰባሰቡት ሙዚቀኞች ቁጥር አርባ ያህል ነበር። ሆኖም ዩኒቨርሲቲው በዚህ እንዲቀጥል ባለመፈለጉና በጀት ባለመመደቡ አሥራ አምሥት የሚሆኑትን ብቻ በማስቀረት ሌሎቹን አሰናበተ። በዚሁ ወቅት ነው በአሥራ ስምንት ዓመቴ ወደ ዩኒቨርሲቲው ቤተ ኪነ ጥበባት ወቴያትር በመሄድ ከኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ጋር የተቀላቀልኩት።

ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን በጊዜው ከነበሩት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የሃገር ፍቅር ቴያትር ቤቶች ለየት የሚያደርገው ቡድኑ ያቀፋቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች በሌሎቹ የሙዚቃ ቡድኖች የሌሉ መሆናቸው ነው። በተለይ ተተኪ ሳይኖራቸው ያለፉት የመጨረሻዎቹ የእምቢልታ ተጫዋቾች የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ አባላት እንደነበሩ ይታወቃል።

የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1969 ወደ አሜሪካ ተጉዞም ለሁለት ወራት ያህል በተለያዩ ክፍለ ግዛቶች በመዘዋወር ትርኢቱን አሳይቷል። በዚህም ወቅት ታዋቂው የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዝግጅቱን አድንቆ ፅፏል። ከዚህም በተጨማሪ በዘመኑ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ባገኘው፣ ከአሜሪካ አልፎ በካናዳና በአውሮፓ ከፍተኛ ተመልካች በነበረው “The Ed Sullivan Show” የተባለ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመቅረብ ችሎ ነበር። በአጠቃላይ ቡድኑ በዘመኑ ከነበሩት ተመሳሳይ የሙዚቃ ቡድኖች አንጋፋውን ሚና ሊጫወት ችሏል።


የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ አባላት ከዩኒቨርሲቲው ከወጣን በኋላ ሺ ሰማኒያ በሚባለው አካባቢ ቤት ተከራይተን እንለማመድ ነበር። ሆኖም ቋሚ የገቢ ምንጭ ስላልነበረን መቸገራችን አልቀረም። ስለዚህም አንድ ቀን የወቅቱን የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አክሊሉ ሃብቴን ጋብዘን የተከራየነውን የመለማመጃ ቦታ አሳየናቸው። እሳቸውም ሁኔታውን ተመልክተው ‘ዩኒቨርሲቲው በገንዘብ ሊረዳችሁ ባይችልም እንኳ የኪነ ጥበባት ወቴያትርን አዳራሽ ለልምምድና ለቢሮ አገልግሎት ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ’ በማለት ስለፈቀዱ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ወደዚያው ሊዛወር ቻለ።


ሆኖም ጊዜው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍና ረብሻ የሚያደርጉበት ነበር። በዚህም የተነሳ ፖሊሶች ወደግቢው እየገቡ ተማሪዎቹን በመደብደብና አልፎ አልፎም በማሰር ያንገላቷቸው ነበር። በዚያ ላይ የተማሪዎች ጥያቄ የጠነከረበት፣ መንግስት ልዩ ትኩረት የሰጠበትና ፖሊሶችም ጥብቅ ክትትል የሚያደርጉበት በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚያስፈራ ነበር። በዚያን ጊዜ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ለተማሪዎችና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በየሁለት ወሩ የሙዚቃ ትርኢት ያቀርብ ነበር። በወቅቱም ግዛቴ ተሾመ የሚባልና ከጎንደር የመጣ ወጣት በኦርኬስትራው ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። ዕድሜው አሥራ አምስት ዓመት ቢሆን ነው። ጥሩ ተሰጥኦም ነበረው። አንድ ቀን እንደተለመደው ፖሊሶች ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተው ተማሪዎቹን ሲያሳድዱ ይህ ወጣት ከተማሪዎቹ አንዱ መስሏቸው በዱላ ደበደቡት። ይህ በሆነ በሁለተኛው ቀን ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ትርኢቱን ለተማሪዎችና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያቀርብ ነበር። ታዲያ ያኔ ግዛቴ በዘፈኑ መሃል እንዲህ የሚል ግጥም ጨመረበት።

“ትተኩሱ እንደሆን፣ ወንድ ይከተላችሁ

ባልረባ ግርግር፣ ሰው ታስፈጃላችሁ።”


ይህን የሰሙትና የልጁን የአዘፋፈን ስልት የወደዱት ተማሪዎች አድናቆታቸውን ባልተቋረጠ ጭብጨባ ከመግለፃቸው በላይ “ይደገም፣ ይደገም” እያሉ በመጮኻቸው ዘፈኑ ሶሥት ጊዜ ተደገመ። የደርግ መንግስት ሲመጣ በግል የሚንቀሳቀሱ የባህል ተቋማት ስለ ተወረሱ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ወደማዘጋጃ ቤቱ የባህልና ቴያትር አዳራሽ ተዛወረ። . . . “

··················

Comments

Leave a comment