ሃገራችን የበርካታ የኪነጥበብ ሰዎች ባለቤት ናት:: ያም ሆኖ ግን በሰሩት ልክ ያልተዘከሩና ያደረጉትን አበርክቶ ያክል ያልተወደሱና ያልተወራላቸውም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም:: ከነዚህ መሃል ታዲያ ለዛሬ በሙዚቃው ዘርፍ ተራማጅ ስራዎችን በመስራትና ለሌሎች አርአያ በመሆን ታላቅ አበርክቶ ስላደረገው የሙዚቃ መምህር የሳክስፎን ተጫዋች የሙዚቃ አቀናባሪና ኮንዳክተር ፈለቀ ሃይሉ በጥቂቱ እንጨዋወታለን::
የአባቱን ፈለግ በመከተል ወደሙዚቃው አለም የተቀላቀለው ገና በልጅነቱ ነው:: በነገራችን ላይ አባቱ ኮሎኔል ሃይሉ ወልደማርያም የታላቁ ክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ በመሪነት (conductor) እና በሙዚቃ ቀማሪነት በርካታ ስራዎችን ያበረከቱ የሙዚቃ ሊቅ ነበሩ:: ከሰሩዋቸው ስራዎች ውስጥ ደግሞ ለአብነት ያክል ኢትዮጲክስ 26 ላይ የተካተቱትን እንደ
“ፍቅር በዘበዘኝ”
“እነማን ነበሩ”
“የሺ ሃረጊቱ”
“ትዝታ”
“ሁሉም በጊዜው ነው” . . . የተሰኙትን የማህሙድ አህመድን ተወዳጅ ስራዎች መጥቀስ ይቻላል::
ወደ ፈለቀ ሃይሉ ስንመለስ የሙዚቃ ትምህርቱን በዋነኝነት የክላርኔት የሙዚቃ መሳሪያን በማጥናት በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በከፍተኛ ማእረግ ያጠናቀቀው በ1969 አ.ም ነበር:: በወቅቱ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ይሰጥ የነበረውን የስኮላርሺፕ እድል በማግኘት ወደቡልጋሪያ በማቅናት የማስተርስ ዲግሪውን ያገኘ ሲሆን በቡልጋሪያ በቆየባቸው 7 አመታት የconducting, music theory, solfeggio, orchestration እና music performance ኮርሶችን ወስዷል::
ፈለቀ የውጪ ሃገር ትምህርቱን አጠናቆ ከተመለሰ በሁዋላ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በዋነኝነት የክላርኔት : ሳክስፎን እና ፒያኖ የሙዚቃ መሳሪያዎችን አጨዋወት እንዲሁም የsolfeggio, Music theory, orchestration, polyphony እና applied music የመሳሰሉትን የሙዚቃ ኮርሶች በማስተማርና በተለያዩ ጊዜያት የወጡ የትምህርት ቤቱ የትምህርት አሰጣጥ ካሪኩለሞች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ለረጅም አመታት ያገለገለ ሲሆን በትምህርት ቤቱ የጃዝ ሙዚቃ ዲፓርትመንት እንዲመሰረት የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ የሙዚቃ ባለውለታም ነው::
ከዚህም በተጨማሪ ከተማሪዎቹ ጋር ሙዚቃን ዝቅ ብሎ አብሮ በመጫወት ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ተመርቀው ከወጡ በሁዋላ በትልልቅ እና ታዋቂ ባንዶች ውስጥ እንዲጫወቱ እድሎችን በማመቻቸት እና ኢትዮጵያዊ የሆነ ሙዚቃ ላይ ጥናት በማድረግ እና በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ኢትዮጲያዊ በሆኑ ቅኝቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ ከፍተኛ ትግልና ተጋድሎ (Not exaggerated) ያደረገ ሙዚቀኛ ነው:: (ትምህርት ቤቱን እስከመልቀቅ ያደረሰው ምክንያትም ይህ ነበር::)
ፈለቀ ከሙዚቃ መምህርነት በተጨማሪም የበርካታ ድምፃውያንን ሙዚቃ በማቀናበር ባንዶችን በመመስረት ሳክስፎን እና ክላርኔትን በላቀ ሁኔታ በመጫወት እና በትልልቅ ኦርኬስትራ የሚሰሩ ሙዚቃዎችን በመፃፍ እንዲሁም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አይዶል ላይ በዳኝነት በመሳተፍታላቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል::
በሃገራችን የሙዚቃ ክስተቶች ላይ የፈለቀን ሚና በወፍ በረር ለመቃኘት የሞከርን እንደሁለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀለው ባንድ ሴይባን ባንድ በመቀጠል ደግሞ አቢሲኒያ ባንድ ይመስለኛል::በ1986 አ.ም ከክብረት ዘኪዮስ እና ደረጄ ተፈራ ጋር በመሆን የኤክስፕረስ ባንድን መስርቷል::የመጀመሪያውን ኢትዮጵያን አይዶል ሾው በዳኝነት መርቶዋል::ከተለያዩ ሙዚቀኞች ጋር በመሆን በበርካታ ሃገራት በመዘዋወር የሙዚቃ ስራዎችን አርቦዋል::Dub Colossus & Samuel Yirga to name the few
ከበርካታ አመታት በሁዋላ ማለትም በ2007 አ.ም ተረስቶ የነበረውን በርካታ ሙዚቀኞች የሚሳተፉበትን የሙዚቃ ባንድ (ሪትራይቭ ኢትዮ ቢግ ባንድ) የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እና የቀድሞ ምሩቃንን እንዲሁም ታዋቂ ድምፃውያንን በማሳተፍ በመመስረት በተለያዩ ቦታዎች ትልልቅ ኮንሰርቶችን አቅርቦዋል::
የአሰፉ ደባልቄን የመጀመሪያ አልበም ሙሉውን
የፋንታሁን ሸዋንቆጨውን ሁለቱንም አልበሞች
ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር በመሆን ደግሞ
የቴዲ አፍሮን – የመጀመሪያ አልበም “ቴዲ”
የነፃነት መለሰን – ፍርቱና
የራሳቸውን የኤክስፕረስ ባንድን – ትውውቅ
የዳዊት መለሰን – አንቺን ነው አልበሞች እና
የፀጋዬ እሸቱን – ተከለከለ አሉ አልበም ከደረጄ ተፈራ እና ሃይለ እግዚአብሄር ገዳሙ ጋር በመሆን አቀናብሮዋል::
ከቅንብር ባሻገር በሳክስፎን እና ኪቦርድ ጨዋታ ከተሳተፈባቸው ስራዎች መሃል ደግሞ
ዳዊት መለሰ – አንቺን ነው አልበም
ቴዲ አፍሮ – ቴዲ አልበም (1st album of Teddy)
ነፃነት መለሰ – ፍርቱና
Dub Colossus- In a town called Addis እና Dub me tender Vol. 1 ከReal world records ጋር
ሳሙኤል ይርጋ – ጉዞ አልበም
አብዱ ኪያር – ጥቁር አንበሳ አልበም
(ሌሎች ስራዎቹን እናንተም ልታግዙኝ ትችላላችሁ)
ፈለቀ ከዚህም በላይ ያልተነገሩ እጅግ ብዙ ስራዎችን ያበረከተ ድንቅ ሙዚቀኛና የሃገር ባለውለታ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ሙዚቀኞች የዛሬ ማንነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ የሙያ አባትም ነው:: ነገር ግን የስራውን ያክል ያልተባለለት በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ላበረከተው ውለታ በምላሹ በደልና ግፍን ያስተናገደ እንዲያም ሆኖ ግን ዛሬም ድረስ ትምህርት ቤቱን እና ተማሪዎቹን ከመውደዱና ከማገዙ ያልቦዘነ በተማሪዎቹ እና የእርሱን ዋጋ በሚያውቁ የሙዚቃ ወዳጆች ዘወትር የሚወደድ እና ተከብሮ የሚኖር ጉምቱ ሙዚቀኛ ነው::
ዛሬ ፈለቀ ኑሮውን አሜሪካን ሃገር ካደረገ 6 ወይም 7 አመታት ተቆጥረዋል:: ምንም እንኩዋን በሩቅ ሆኖ እንደበፊቱ ሙዚቃው ላይ አሻራውን ማሳረፍ ቀላል ባይሆንም ዛሬም ከሙዚቃ አልራቀም ሙዚቃን ያስተምራል ያቀናብራል ከተለያዩ ባንዶች ጋር ሳክስፎኑን ይጫወታል:: የቀድሞ ተማሪዎቹን ማበርታት እና ማገዙ ላይም ቢሆን ደከመኝ ብሎ አያውቅም:: በቅርቡ የራሱን የሙዚቃ አልበም እንደሚያደርሰንም እንጠብቃለን::
የፈለቀን ስራዎች እንዘርዝር ቢባል አንባቢን ማድከም ይሆናልና እንዲያው በግርድፉ አለፍ አለፍ ብዬ ነው ከማውቀው ጥቂቱን አሳጥሬ ላስቃኛችሁ የሞከርኩት:: ደግሞ ያልተነገረውን ሳላካትት የዘነጋሁትን እና እናንተም ማለት የምትፈልጉት ካለ ልትጨምሩበት ትችላላችሁ:: ስህተት ካለም እታረማለሁ::የእኔን ፅሁፍ እንግዲህ በዚህ አበቃለሁ::
“ፈለቀ ሃይሉ አንተ የማትሸነፈው ድንቅ የጥበብ ሰው ላደረግክልን ውለታ ሁሉ በተማሪዎችህ እና ሙዚቃን የእውነት በሚያከብሩት ስም አመሰግንሃለሁ:: በመልካምነትህ ያኖርከው አሻራና ስንት ትንታግ ሙዚቀኞችን አፍርቷል መሰለህ:: ረጅም እድሜና ጤና ላንተ ይሁን”
© MikiMac
Leave a comment