ለመልካም 74 ዲጂታል መጽሄት የተጻፈ
በMikiMac
ቀደም ባሉት ዘመናት ሙዚቀኞቻችን ሙዚቃዎቻቸውን በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም አውድአመትን ጠብቀው በየቴአትር ቤቱ በሚሰናዱ ሁነቶች ላይ በማቅረብ ከአድማጭ ተመልካቹ ጋር ይገናኙ ነበር። ከዚያም አለፍ ሲል ሙዚቃቸውን በሸክላና በካሴት ዘመን ሲል ደግሞ በሲዲ ቀድተው እና አስቀድተው በቁጥር ለበዛው አድማጭ ያዳርሱት ነበር።
በዚህ ሁሉ መሃል ብዙ ውጣ ውረዶችን ያለፉ የሙዚቃው ባለድርሻ አካላት አሁን ያለውን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከቀደመውም የከፋና አይነተ ብዙ ችግሮችን ይዞ ብቅ እንዳለ ሲያማርሩ ይሰማል። ከእነዚህ ችግሮች ዋነኛውና ቀዳሚው ደግሞ ለዘርፉ አስተዋጾ ያበረከቱ፣ የሙዚቃ ባለሙያዎች የድርሻቸውን ሳያገኙ መቅረታቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሙዚቃ አሳታሚ የሚል ስም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችን ብቻ ተጠቃሚ ያደረገው ስርአት ለሙዚቃው አስተዋጾ ያበረከቱትን ባለሙያዎች ሲዘነጋ ይታያል። እንዲያው የድርሻውን እኩሌታ ያገኘ ቢባል እንኳን ከዘፋኝ የዘለለ አይደለም። እንዲያውስ ለቅጂና ተዛማጅ ጉዳዮች እሰራለሁ ሲል የምናውቀው ቢሮ እንጂ ስርአቱ እንኳን ኖሮን አያውቅም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዘፋኝ አልበም ገዝተው እንደ ሸቀጥ በጅምላና ችርቻሮ የሚሸጡትን ከሙያው ጋር መንገድ ላይ እንኳን የማይተዋወቁ ባለገንዘብ ነጋዴዎችንም ማስተዋል የተለመደ ነገር ሆኗል። ይሄ ሁሉ እንቆቅልሽ የተሞላበትን ሙዚቃችንን ለማሳደግ ነው እንግዲህ ያለማንም ደጋፊነት ሙዚቀኛው ብቻውን ሲደክም የሚታየው። ከሰሞኑ አገልግሎት መስጠት የጀመረው እና አውታር የተባለው የሙዚቃ መሸጫ መተግበሪያም ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። እንደ ኤልያስ መልካ ያሉ እድሜያቸውን ለሙያው የሰጡና የግብራቸውን ልክ ያህል እንኳን ክብር ያልተሰጣቸው እውነተኛ የሙዚቃ ሰዎች የዘየዱት መላ ነው እንግዲህ አውታር ማለት።

በሰለጠኑት እና ኢንተርኔት እጅጉን ርካሽ በሆነባቸው ሃገራት እንደ Amazon music, Apple music, Deezer, Tidal, Spotify, YouTube Music, Google music . . . የሚባሉ ሰዎች በየወሩ የተወሰነ ገንዘብ እየከፈሉ ሙዚቃን ያለምንም ገደብ የሚያዳምጡባቸው መተግበሪያዎች ብዙ ናቸው።አውታርም ታዲያ ከዚህ ብዙም ያልተለየ አገልግሎት ነው ለሙዚቃ አዳማጩ ይዞ የመጣው። ለሙዚቀኛው ደግሞ የድርሻውን ልክ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ የሚያገኝበት። ምንም እንኳን የሃገራችን የኢንተርኔት ዋጋ አለም ላይ ውድ ከሚባሉት አንዱ መሆኑ፣ የዲጂታል ገንዘብ ልውውጥ ብዙም የተለመደ ያለመሆኑና አገልግሎቱን ለማግኘት የስማርት ስልክ የሚጠይቅ መሆኑ ስራውን ፈታኝ የሚያደርገው ቢሆንም ነገር ግን በጊዜ ሂደት የሚለመድና አገልግሎቱም እየተሻሻለ እንደሚሄድ እርግጥ ነው። ስለ አውታር እንግዲህ በየሚዲያውና የማህበራዊ ድህረ ገጹ ከበቂም በላይ ብዙ ስለተባለለት የምለው ነገር አይኖርም። በፍጹም አውታር ስለሚባል ነገር አልሰማንም የምትሉ ካላችሁ ደግሞ ፌስቡክ ላይ በመሄድ Awtar Multimedia የሚለው ፔጃቸው ላይ ዘርዘር ያለ መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ።
• ሙዚቀኞቻችን ኮፒራይት ስለሚባለው ነገር ያውቃሉ ወይ? የሚያውቁ ከሆነ ደግሞ ጥቅማቸውን ስለምን አሳልፈው ይሰጣሉ?
ይህንን የምለው ያለምክንያት አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰሩትን የሙዚቃ አልበም ለአሳታሚ ከሸጡ በኋላ አድማጭ በማጣት ይሁን ከግንዛቤ ማነስ በማይገባኝ ሁኔታ ሙሉ አልበሙን በወጣ በሳምንታት ውስጥ ሙሉውን አልበም YouTube እና Telegram ላይ ሲለቁት ተመልክቻለሁ። ይህ ማለት ደግሞ ተስማምተው የሸጡለትን አሳታሚ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ገቢውን እያሳጡት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከላይ በጠቀስናቸው በመላው አለም ባሉ እንደ Apple music, Spotify, CDbaby, amazon music, Google music . . . ካሉ ከሙዚቃ ገቢ ማግኛ መተግበሪያዎች የሚያገኙትን ገቢ በፍቃዳቸው እንደመተው አይቆጠርም ትላላችሁ? የሙዚቃ አድማጩስ ሙዚቀኛው በነጻ የለቀቀለትን ሙዚቃ ማዳመጥ እየቻለ እንዴት ገንዘብ አውጥቶ አልበም ይገዛል?
• መንግስት የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ ምን ያክል ያውቀዋል? ከሙዚቃው ኢንዱስትሪስ ሃገሪቱ ምን ያክል ገቢ እያጣች ነው?
ቴዎድሮስ ተክሌ በሙያው የሳውንድ ኢንጂነር ሲሆን ነዋሪነቱ ደግሞ አሜሪካን ሃገር ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ነው። «የሃገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በተለይም የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥሰቱ ሃገሪቱን እጅግ የላቀ ገቢ እያሳጣት ነው ለዚህ ደግሞ መንግስትም ሆነ ይመለከተናል የሚሉት ባለድርሻዎች የሚሉትን ያክል አልሰሩም» ይላል። ከሙዚቃ ሃገራት ስለሚያገኙት ገቢ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል። «ያደጉት ሃገራት በአመት በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ግብር ከሚሰበስቡበት የገቢ ምንጫቸው ውስጥ የመዝናኛው ዘርፍ አንዱ ነው። ሙዚቃ ደግሞ ከዚህ ውስጥ ዋነኛው ሲሆን ከፍተኛውን አመታዊ ግብር በማስገባት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል» ይላል። «ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በ2017 የፈረንጆቹ አመት ብቻ አሜሪካ ከሙዚቃው ዘርፍ 17.3 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንዳገኘች ይገልጽና ይህ የሙዚቃው አብዮት ምን ያክል ሃብት ማምጣት እንደሚችልና የዳበረ የሙዚቃ ገበያ ስርአት በመሰረቱት ሃገራት የሙዚቃው አብዮት ምን ያክል ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅስ ያሳያል» ሲል ሃሳቡን ያጋራል።
ታዲያ ለዛሬ በዋናነት ከሙዚቀኞች የጥቅም ክፍፍልና የመብት ጥያቄው ጎን ለጎን ብንወያይባቸው መልካም ናቸው ብዬ የማስባቸውን የተወሰኑ ነጥቦች ለማንሳት እሞክራለሁ።
ሃገራችን ኢትዮጵያስ ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ በተለይም ከሙዚቃው የምታገኘው ወይስ የምታጣው በዝቷል ?????????
ይህ ማለት የሃገራችንን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከአሜሪካን ጋር እናወዳድረው ማለት ባይሆንም መንግስት ትኩረት ቢሰጠውና ድጋፍ ቢያደርግለት፣ ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን የሚሸጡበት እንደ አውታር ያሉ በአይነት እና በቁጥር የበዙ መላዎች ቢበጁለትና ለስነጥበባዊ ስራዎች በአግባቡ ጥበቃ የሚያደርግ ከወረቀት የዘለለ የህግ ከለላ ቢሰናዳላቸው ሃገሪቱ ለውጪ ባለሃብቶች መሬት እየሸነሸነት በመሸጥ ከምታገኘው ገቢ ያልተናነሰ ገንዘብ ማንቀሳቀስ የሚችል ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው ባይ ነኝ።
የመብት ጥያቄና የጥቅም ክፍፍል ሲነሳ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች እና የዜማና ግጥም ደራሲያንን የሚያካትት አሰራር ሊኖረን ይገባል። ለዘመናት በችግር ሲባክኑ የኖሩትን አያሌ የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲያንን ኑሮ በየሚዲያው ስንሰማ ኖረናል። የእነርሱን ስራ ሰርተው ከከበሩ ዘፋኞችና አሳታሚዎች ደጅ እየጠኑ፣ ሲታመሙ ህዝብ ዘንድ ቀርበው እርዳታ እየጠየቁ የስራቸውን ኩርማን እንኳን ጥቅም ያላገኙ የሙዚቃውን የጀርባ አጥንቶች በእኩልነት ያልጠቀመ ስርአት ሚዛናዊ ነው ብዬ አላምንም። አውታርም ቢሆን ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያሉ ሙዚቃዎችን መተግበሪያው ላይ እንዳካተተ የሰማን ሲሆን ይህንን ጉዳይም ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
ለሙዚቃችን እድገት (ቁልቁለት የሚሉም አይጠፉም) የኢንተርኔት አብዮቱ ይዞብን እና ይዞልን ከመጣቸው ተግዳሮቶችና ጥቅሞች መካከል YouTube አንዱ ነው። ዩትዩብ ላይ ቪዲዮዎችን በመጫን ገንዘብ የማግኘትን ቢዝነስ ተከትሎ በሃገራችን ከተጀመሩት ዘርፎች ውስጥ ደግሞ የሚወጡ ሙዚቃዎችን ቻናላቸው ላይ ጭነው ገንዘብ ማግኘት (YouTube Monetization) ነው። እነዚህ ባለብዙ ተከታይ የዩትዩብ ቻናል ባለቤቶች የገቢያቸውን ማደግ ተከትሎ ሙዚቃና የሙዚቃ ቪዲዮ ፕሮዲውስ እስከማድረግ ሁሉ ደርሰዋል። ታዲያ እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ የሙዚቃ ቪዲዮ YouTube ቻናል ባለቤቶች የሙዚቃውን ገበያ እጅግ ከመቆጣጠራቸው የተነሳ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ላይ ጫና ማሳደራቸው አልቀረም። ይህንንም ተከትሎ ለዘፈን የሚሰሩ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን በማየት ፋንታ ለቪዲዮ የሚዘፈኑ ዘፈኖችን እስከማዳመጥ ሁሉ ደርሰናል። ሙዚቀኞችም ለአድማጭ ለመድረስ ሲሉ ብቻ የሙዚቃ ቪዲዮ መስራትን አማራጭ የሌለው መንገድ ሲያደርጉት ሁሉ እየተስተዋለ ነው። በእርግጥ የሙዚቃ ቪዲዮ መስራት ክፋት ባይኖረውም ነገር ግን ጥሩ ሙዚቃ እያላቸው የሙዚቃ ቪዲዮ ቢዝነሱ ሰማይ ከመድረሱ የተነሳ በገንዘብ እጥረት ሙዚቃቸውን ማስተዋወቅ ያልቻሉ በርካታ ሙዚቀኞች ብሶታቸውን ሲያሰሙ ይስተዋላል። ይህም ብቻ ሳይሆን በነዚህው የዮትዩብ ቻናሎች አማካኝነት ከሚሰራጨውን የሙዚቃ ቪዲዮ ገቢ 100% ያለምንም ተቀናቃኝ ኪሳቸው የሚያስገቡትም እነዚህው የዩትዩብ ቻናል ባለቤቶች ናቸው። ይህ ስራ ለተወሰኑ የጥቅም ተጋሪዎች (በተለይም ለዩትዩብ ቻናሎቹ ባለቤቶች እና በሙዚቃ ቪዲዮ ፕሮዳክሽን ለተሰማሩት) ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ለጀማሪ ሙዚቀኞችም ስራቸውን ለህዝብ ማድረሻ ቀላል መንገድም ጭምር ነው። ነገር ግን በፈቃዱ ብዙ አድማጭ ለማግኘት መብቱን አሳልፎ እየሰጠ ያለው ሙዚቀኛ የመብት ጥሰት እየተፈጸመብኝ ነው ብሎ ሌሎችን መውቀሱስ ተገቢ ነው ትላላችሁ?
የራዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎቻችን የመብዛታቸውን ያክል ለሚያጫውቱት ሙዚቃ ተገቢውን ክፍያ ይከፍላሉ ወይ? በእርግጥ የሚዲያ ነገር ሲነሳ ብዙዎች ራስን ከማስተዋወቅ ጋር የሚያያይዙት ቢሆንም ነገር ግን ሚዲያዎች ሙዚቃን ከማጫወት ከሚያገኙት ገቢ ላይ ሙዚቀኛውን ተጠቃሚ ማድረግም ይኖርባቸዋል። የሚዲያ ተቋማት ሙዚቃን ተጠቅመው ወይም በየዝግጅቶቻቸው ጣልቃ ሙዚቃ እንደማጫወታቸው ሁሉ እያንዳንዱ የአየር ሰአታቸውም ቢሆን ከስፖንሰሮች እና ማስታወቂያ የሚያገኙትም ገንዘብ ቢሆን ዳጎስ ያለ ነው። ታዲያ ይህን ያክል ገቢ ከሚገኝበት የሚዲያ ቢዝነስ ለሬዲዮና ቴለቪዥን ድራማዎች የሚወጣውን ሽራፊ ገንዘብ እንኳን ለሙዚቃ ሲባል ሰምተን አናውቅም። በሌሎች ሃገራት ከላይ እንደቃኘናቸው የሙዚቃ ማሰራጫዎች ሁሉ የትኞቹም የራዲዮም ሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች (ዲጄዎችንም ያካትታል) ለሚያጫውቷቸው ሙዚቃዎች ሁሉ ለሙዚቃው ባለቤቶች የመክፈል ግዴታ አለባቸው። ይህን ተከታትለው ለሙዚቀኞቹ ክፍያ እንዲፈጸም የሚያደርጉ ደግሞ በርካታ ድርጅቶች አሉ። ይህም በዘርፉ ፍትሃዊ የጥቅም ተጋሪነትን የሚያዳብር ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ያሉ የሙዚቃ ኤጀንሲዎች እና የግል የሙዚቃ ኮፒራይት መብት ጥበቃ አካላት እንዲፈጠሩና የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ወደኛስ ሃገር ስንመጣ? ምላሹን ለእናንተው እተወዋለሁ። ለዛሬ በዚህ አበቃለሁ። ሁሉንም ባይሆን ዋና ዋና ያልኳቸውን ሃሳቦች ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። እዚህ ጽሁፍ ላይ የቀረቡ ሃሳቦች በሙሉ የግል አስተያየቶች ሲሆኑ የጽሁፉም አንድምታ ማንንም ለማሳነስ አልያም ለመውቀስ ሳይሆን በግሌ ስለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ያለኝን እይታ ለማጽባረቅና የእናንተንም ግብረ መልስ ለመስማት ያክል የቀረበ ነው። ሃሳብና አስተያየታችሁን እንዲሁም ተሳስተሃል ታረም የሚል ወቀሳም ጭምር ካለ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
ይመቻችሁ
💛💛💛
Leave a comment